የአማርኛ ልቦለዳዊ አቀራረብ ባላቸው ነገር ግን በዚያ ብቻ ሊወሰኑ በማይችሉ እመጓና ዝጎራ በሚባሉ ሁለት መጻሕፍት የምናውቀው የሥነ ምሕዳር ሳይንቲስቱ ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ዛሬ ደግሞ አነጋገሪ እንደሚሆን በምገምተው ሦስተኛው መጽሐፉ በመርበብት ወደየደጃችን በጣም ቀርቦ ማንኳኳት የጀመረ ይመስለኛል።አዲሱ መጽሐፉ በሦስተኛ መደብ ተራኪ የቀረበ ቢሆንም በሁለቱ መጻሕፍት የምናውቀው አንደኛ መደብ ተራኪና ዋና ገጸ ባሕርይ የነበረውን ሲሳይ የተባለውን ገጸ በሕርይ ግን ለሦስተኛ ጊዜ ይዞት መጥቷል። አንድን ገጸ ባሕርይ በተከታታይ የአንድ ሰው ሥራዎች ላይ ማምጣት ከዚህ በፊት በሌላው ዐለም የታወቀ ቢሆንም ይህን ያደረገበት ምክንያት ብቻ ሦስቱንም አንድ ጊዜ አንብበን የመጻሕፍቱን ጭብጥ እንደገና እንድንፈልግ ሙያዊ ብቻ ሳይሆን የተጠቃሚነት ግዴታም ሳያመጣብን አልቀረም። በመርበብት መግዛትና መገዛት፡ ኃይለ መንፈስና ኃይለ ዕፅ፡ ነጭና ጥቁር፡ ጣልያንና ኢትዮጵያ ይተሣሠራሉ። ኃይለ ዕፅንና ኃይለ መንፈስን፤ ማግኘትንና መጠቀምን ዓላማና ግብ ያደረገ የነጭና የጥቁር፣ የእምነትና የጉልበት፣ የዕውቀትና ዕውቀት መሰል ድንቁርና(ignorance)፣ የእውነትና የእውነት መሰል ሐሰት ጦርነት ሲያካሒድበት ይመለከታሉ።ከዚህም በላይ በምዕራባዊው የትምህርትና የፍልስፍና መሠረት ላይ ብቻ የተቃኘውን የሥነ ጽሑፋዊ ተዋሥኦም ጥያቄ እያቀረበበት ይመስላል። አንድ ሥነ ጽሑፍ የሚጻፈው ለምንድን ነው? ደረጃውና ጥቅሙስ የሚለካው በምንድን ነው? የሥነ ጽሑፋዊ ውበት መለኪያውስ ምንድን ነው? ከሥነ ጽሑፍ ሊገኝ የሚገባውን አስተዋጽኦስ የሥነ ጽሑፍ ዲግሪ ላላቸውና ለዚህ ዕውቀት ቀረቤታ ወይም መረዳት ላላቸው ብቻ መተው ተገቢ ነው? ለምርምራዊ ዕውቀትና ጽሑፎች ተደራሽ ሊሆን የማይችለውን አብዛኛውን ማኅበረሰብ በሥነ ጽሑፍም ከምናገልለው ለእርሱ በሚሆን መንገድ አቅርበን የጥበብና የዕውቀት ተቋዳሽ እና የመኅበረሰብ ሥሪት ተሳታፊ ለምን አናደርገውም? ካለዚያማ ምሁራዊ ሳይሆን ፓለቲካዊ ለሆኑ የታሪክ ትርክቶችና ስለ ሴራ በሚናገሩ የሴራ ጽሑፎች ካጋለጥነው በኋላ መልሰን እንዴት ልንነቅፈው እንችላለን የሚሉ ሙግቶችን በግልጽና በተዋሥኦ ሳይሆን በራሱ ሥነ ጽሑፋዊ አቀራረብ ለመሞገትም የተነሣ ይመስለኛል። በርግጥም ጽሑፎቹ ቀላልና ተደራሽ ወይም ለአብዛኛው ተነባቢ ናቸው። ነገር ግን ስውሩን ነገር በተማሩት ትምህርትና በአከማቹት ዕውቀት ለሚፈክሩ ሃያስያን በለመዷቸው በሮች ገብተው ሊያገኟቸው የሚያስቸግሩ የመሰሉኝን ሌሎች ሥውር ሙግቶችንም የሚያነሡ፣ ደጋግመን እንድናነብብ የሚገፋፉ መሆናቸውን በተለይ በዚህ በሦስተኛው መጽሐፉ ገለጥለጥ አድርጎ ያቀረበ ይመስለኛል።ከመንፈስ ጋር የተገናኘ ታሪክን ማዕከል ያደረገው መርበብት ስለመታሠርና መገዛት ይናገራል። ከባዱ ጥያቄ ግን የታሠረው ማን ነው የሚለው ነው? የተማረው ወይስ ያልተማረው? ርኩስ መንፈስስ የሚዋረሰው በየት በኩል ነው? በዛር ከተዋረሰውና በዲግሪ ከተዋረሰው የትኛው ቶሎ ይለቃል? መንፈስን ከሚገዙት ነን ወይስ መንፈሱ ከሚገዛቸው? እነዚህን መሰል ጥያቄዎች የሚያስነሣ ከእውቀትና ከትውፊት ሳይጣላ ነገረ ዕውቀታችንን እንድንፈትሽ የሚጠቁም ከመንፈስ ነጻ ነኝ የምለው ሁሉ በማያውቀው ሌላ መንፈስ መያዙን የሚጠቁም፣ ወደ አስተሳሰብ ደጃችን በጣም ተጠግቶ የሚያንኳኳ ድንቅ መጽሐፍ ነው። በእኔ እምነት ልክ እንደ እመጓ ሁሉ ለማቋረጥ የሚቸግር እንቅልፍ ከልካይ መጽሐፍ ፤ መርበብት።ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ(በሥነ ድርሳን ሁለተኛ ዲግሪ)