ማን ይናገር የነበረ᎐᎐᎐ የታኅሣሡ ግርግር እና መዘዙ በሚል ርዕስ አቶ ብርሃኑ አስረስ ያቀረቡልን መጽሐፍ ዋነኛው ትኩረቱ በ፲፱፻፶፫ ዓ᎐ም᎐ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ላይ ሲሆን፤ እሳቸው በቦታው ስለነበሩ፣ ተካፋይም ስለሆኑ፣ ያዩትንና የሰሙትን ትውስታቸውን ያቀረቡበት ነው። ይህ መጽሐፍ አያሌ፣ ከዚህ በፊት የማይታወቁ፣ ኩነቶችን አቅርቦልናል። ከነርሱም መካከል ስለኮሌኔል ወርቅነህ፣ መፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ እንዲደረግ ምክንያት እንደሆነች በተለያዩ ጸሐፊዎች የተነገረላት ቴሌግራም ጉዳይ እና የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ሲካሔድ በኮ/ል ወርቅነህና በጀነራል መንግሥቱ መካከል ስለነበረው የስልት ልዩነት የገለጹልን ይገኙበታል።᎐᎐᎐ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፣ ኮሎኔል ወርቅነህን ከክብር ዘበኛ መኮንንነት አንስተቅ የልዩ ካቢኔያቸው የደህንነት ሹም ያደረጉት በ፲፱፻፵፱ ዓ᎐ም᎐ ነበር። ከዚህ ወቅት እስከ መፈንቅለ መንግሥቱ ድረስ ያለው ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ ወርቅነህ ብዙ ጉዳዮችን ያከናወነበት ወይም ቢያንስ ለውይይት ያነሣሳበት ነበር ማለት ይቻላል። የመሬት ይዞታ ነገር በአእምሮው ውስጥ ይጉላላ እንደነበርና የሪፎርም አስፈላጊነትን አምኖበት እንደነበር ከብርሃኑ ትረካ በግልጽ ማየት ይቻላል።᎐᎐᎐ ደራሲው ለወርቅነህ እጅግ በጣም ታማኝ ስለነበሩ (ይህም በጣም የሚያስደንቀው ባህርያቸው ነው!)፣ አለቃቸው የትና እንዴት እንደወደቀ ሥራዬ ብለው ተከታትለው ለማጣራት ሞክረዋል። ገለጻቸው፣ ሌሎቹ ባጭሩ ያቀረቡትን ምስክርነት አስፋፍቶ ያቀርባል፤ የተሻለም ተአማኒነት አለው፤ ስለዚህ፣ ስለኮሎኔሉ አሟሟት ከአሁን በሁዋላ እርግጠኛ ሆኖ መጻፍም ሆነ ማውራት ይቻላል።᎐᎐᎐ መፈንቅለ መንግሥቱ ውስጥ በመካፈላቸው ለአያሌ አመታት ታሥረው ከተፈቱ በሁዋላ፣ አቶ ብርሃኑ ጉዳዩን ሲከታተሉ ቴሌግራሟን አግኝተዋት ኖሮ፣ በመጽሐፋቸው ውስጥ የፎቶ ግልባጭ ከተዋል፤ በትረካቸውም ውስጥ ይጠቅሷታል። ለመጀመሪያ ጊዜ አንባቢም ያያታል፤ ይልቁንም ዘመኑን የሚያጠኑ የታሪክ ጸሐፊዎች ቀረብ አድርገው እንደሚያተኩሩባት አይጠረጠርም።᎐᎐᎐ የወርቅነህ ሐሳብ በአስቸኳይ አንድ መቺ ኃይል ወደ አራተኛው ክፍለ ጦር ኮማንድ ፓስት (መሿለኪያ አጠገብ) ሔዶ፣ እዚያ ያሉትን ጄኔራሎች ቢቻል መያዝ፣ ካልተቻለ መደምሰስ አለበት የሚል ነበር። ይህንን የኮማንዶ ኦፕሬሽንም ካስፈለገ ራሱ ለመምራት ዝግጁ እንደሆነም ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ጄኔራል መንግሥቱ በማያወላዳ ምክንያት፣ አልተቀበለውም፤ ጉዳዩም በዚህ ተዘጋ። ይህ አለመግባባት ወርቅነህ ጐበዝ፣ ፈጣንና ብሩህ አእምሮ የነበረው ሰው እንደነበረ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ስለእርሱ ተክለ ሰውነትና ችሎታ ዘመነኞቹ ይሉት የነበረውን ሁሉ የሚደግፍ ይሆናል ፤ እውነትም፣ ወርቅነህ ቀላል ሰው አልነበረም፤ እውነትም፣ አፄ ኃይለሥላሴ ሰው መምረጥ ያውቃሉ የሚያሰኝ ነው።ባጭሩ፣ ይህ ሥራ የ፳ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን የፓለቲካና የማህበራዊ ታሪክ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች በእጅጉ ሊጠቀሙበት የሚችሉት መጽሐፍ ነው።ሺፈራው በቀለ የኢትዮጵያ ታሪክ ፕሮፌሰርአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ