የለበሰችው ጃኬትና ሱሪ ወንድ ቢያስመስላትም ረጂም ፀጉሯ ሴትነቷን ይናገራል። በድንገት ትከሻዋን ሰው ነካት፣ በፍጥነት ዞር አለች።"መፋቂያሽ ከየት ተላከልሽ?" አላት እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ። ደንገጥ ብላ እጇን ከኪሳ አወጣችና፣"ከጃማይካ" ብላ ጨበጠችው።* * * *አልጋዋ ላይ ተጋደመቸ፡ ደግሞ በደረቷ ትራሱን ጭንቅላታ ላይ ጫነች። መረጋጋት ግን አቃታት፡ የሆነው ሁሉ ሊሆን የሚችል መሆኑን ብትቀበልም፣ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ብትሆንም ለእንዲህ ዓይነት የሃዘን ስሜት ግን ዝግጁ አልነበረችም። የሚመጣውን ሁሉ በቀላሉ የምትቀበል ይመስላት ነበር፣ ልትቀበለው ግን አልቻለችም። በላይሁን ከአይኖቿ አልሰወር አላት፡ አስቻለውን አስታወሰችው እናቱንም አሰበቻቸው። ቅዱስ አብሯት እንዲሆን ፈለገች፡ አጠገቧ ሆኖ አይዞሽ እንዲላት "ያለመስዋዕትነት ድል የለም!" ብሎ እንዲያበረታታት ተመኘች። አንተነህ ግጥሞቹን እንዲያነብላት፡ የትግል ታሪኮችን እንዲነግራት... ሀሳቧ ትርምስምስ አለባት። ጋዲሻና ዘርዓይ ከሀሳቧ አልጠፋ አሏት፡ "ይህን ጊዜ የት ይሆኑ? ምንስ እያደረጉ ይሆን?" ጥያቄዎቹ ሰላም አልሰጥ አሏት። ትራሱን ወረወረችና ተነሳች፡ ፊቷን ጠራረገችና ሰዓቷን ተመለከተች። ወደነበላይሁን ቤት ለመሄድ ራመድ ስትል ምን ብላ እንደምታጽናናቸው ጨነቃት።* * * * "ለአገር መሥራት በፓለቲካ ብቻ ነው ያለው ማነው? በሕይወታቸን እያንዳንዱ ቀን አንድ በጉ ነገር ማበርከት መቻል ላገር መሥራት ነው!"* * * * "ቢያንስ በሙያችን ለዓላማ የምንኖር መሆን አለብን፡ ለሕዝብ አስቦ ሕይወቱን የሰዋ ትውልድ አካል በመሆናችን ፓለቲካው ባይሳካልንም በሙያችን የጓዶቻችንን ዓላማ ተከትለን ለህዝብ አገልጋይ መሆን ከቻልን ባለዕዳነታችንን ከሕይወት መስዋእትነት በመመለስ ለመክፈል እንችላለን