...የሀገር መሪዎች፣ የሃይማኖት እና የእምነት መሪዎች፣ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ አንቃዒና አንቃሂ ሊሆኑ ይገባቸዋል። አንቃዒ ሕዝቡን የሚያነቃ፣ ንቅሐተ ኅሊና የአስተሳሰብ ንቃትን የሚፈጥር፣ ቅንነትና መልካምነትን አፍላቂ ነው። ለመልካም አስተሳሰብ መንገድ ሠንጣቂ፣ መንገዱን የሚያውቅ፣ በመንገዱም የሚሄድና ለሌሎችም ቅን የሆነውን መንገድ አንቅቶ የሚያሳይ ነው። ይህ ይፈጸም ዘንድ መሪዎች በኣንቃዒነት ላይ አንቃሂነትን መደረብ አለባቸው። አንቃሂነት የተኛውን መቀስቀስ ነው፣ የሞተውንም ማስነሳት ነው። ሕዝብ አስነሺ ይሻል። በሐሳብ እንዳይሞት አንቅሆ ያስፈልገዋል። የመሪዎች፣ የአስተዳዳሪዎች ብሎም የመምህራን ኃላፊነት፦ ሕዝብ የትናንት ማንነቱን ረስቶ፦ በዛሬ ከንቱነት ፈዝዞ የነገ አሳቢ እንዳይሆን ከያዘው የኅሊና እንቅልፍ ይነሣ ዘንድ አንቃሒያን መሆን ይገባቸዋል። ይልቁንም ለዛሬይቱ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ይህ የግድ ነው።...ከመጽሐፉ ውስጥ ገጽ የተወሰደመምህር ዶክተር ዘበነ ለማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መምህረ ሃይማኖት፦ የቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ከንባብ እስከ ትርጓሜ፦ ሥርዓተ ቅዳሴን ከታላቁ ብፁዕ አባት አቡነ ሰላማና ከታላቁ ሊቅ ከመጋቤ ምሥጢር አለቃ መሠረት ተሰማ የተማሩ። በነገረ መለኮት ትምህርት ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በማስተርስ ዲግሪ ስለዓለም እምነቶች ጥናትና ፍልስፍና በሀዋርድ ዮኒቨርሲቲ፣ በዶክተሬት ዲግሪ በሥነ አመራር እና አንትሮፓሎጂ ጥናት ከሀዋርድ ዮኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ ተምረው ፈጽመዋል።በአሁኑ ሰዓት በቡዊ ስቴት ዮኒቨርሲቲ በአጃንከት ፕሮፌሰር በሀዋርድ ዮኒቨርሲቲም ገስት ፕሮፌሰር ናቸው። በሊሊ ኢንዶመንት በሚደገፍ ቴዎሎጂካል ኢጁኬሽን(Theological Education between the Times) በምርምር ሥራ፣ CEOS ለተባለ አሜሪካን ድርጅት በቦርጅ አባልነት እያገለገሉ በተጨማሪ በዋናነት በአሜሪካን ሀገር በደብረ ገነት መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድብሩ አለቃ ናቸው። እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለግላሉ። ኑሮአቸውም ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ኅሊና ታደሰ ጋር በአሜሪካን ሀገር በቨርጂኒያ ግዛት ነው።