ትውልዱ አስደናቂ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሳይንሳዊ ዕውቀት እየረሳ በመጣበት እንዲሁም የውጪ ዕውቀትን ፍለጋ ብቻ በሚባዝንበት በዚህ ወቅት ዘመናዊ አስትሮኖሚን (የሥነ ከዋክብትን የሥነ ፈለክን) ዕውቀት ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከነበራቸው የአስትሮኖሚ ዕውቀት ጋር በማጣጣም የተሠራ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ልዩና ድንቅ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የጥንት ኢትዮጵያውያንን የመጠቀ የሕዋ ሳይንስ ዕውቀት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። በመሆኑም ይህን መጽሐፍ የሚያነብ ማንኛውም አንባቢ በእውነት ሀገራችን ከብዙ ሺሕ ዓመታት በፊት በአስትሮኖሚ ጥናት የት ደረጃ እንደነበረች ግንዛቤን ስለሚሰጥ አሁን ያለው ትውልድ ለምን አሁንስ? ብሎ እንዲጠይቅ አድርጎ ቁጭትን የሚፈጥርለት መጽሐፍ ነው።ሁሉቱም የዚህ መጽሐፍ አዘጋጆች ዶክተር ሮዳስ ታደሰና ዶክተር ጌትነት ፈለቀ በሙያቸው፣ በዕውቀታቸው አንቱ የተባሉ በመሆናቸውና ረጅም ጊዜ ወስደው የሠሩት ድንቅ ሥራ በመሆኑ የዚህ መጽሐፍ አንባብያን በታሪክ ወደኋላ በመመለስ የአባቶቻችንን የታላቅነት ደረጃ ማየት እንዲችሉና ዓለም በጊዜያችን የደረሰበትን የሥነ ፈለክ ሳይንስን በትክክል እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል።ይህ መጽሐፍ ከ4000 ዓመታት በፊት በሃገራችን ንጉሣውያን ቤተሰቦች ስለተሠየሙ ሕብራተ ከዋክብት ፤ የዓለም ሳይንቲስቶች ሁሌም ስለሚመረምሩት ስለ ጨለማው ጉድጓድ (Black Hole) ምስጢር፣ መላው የዓለማችን ሕዝብ "አሉ? ወይስ የሉም?" በማለት ስለሚጠይቃቸው ስለ ሕዋ መጤ ፍጡራን (Aliens) በዝርዝር ይዟል። ስለ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ፕላኔቶች፣ ድንክ ፕላኔቶች የመሳሰሉትን ሰፊ የሕዋ ሳይንስ ሐሳቦችን ያነሣል። በተጨማሪም ሁሉም ሊያውቀው ስለሚገባው አስደናቂውን የኢትዮጵያን የዘመን አቄጣጠር በጥልቀት ይዳስሳል። የዚህ መጽሐፍ ይዘቱ ሁሉንም አናባቢዎች ማዕከል ያደረገ ዘመናዊውንና ሃገር በቀል አስትሮኖሚን አዋሕዶ የያዘ በመሆኑ ሁሉም ሰው ቢያነበውና ቢማርበት ትውልዱን በሚገባ የሚቀርጽ ድንቅ መጽሐፍ ነው ብዬ አምናለሁ።ጌታቸው መኮንን መንግሥቴ(ዶ/ር)(PhD. Astrophysics, (South African Institute of Physics))