ረቂቁን ተቀብዬ ነገረ ጉዳዩን ለመቃኘት ያህል ብቻ ድንገት የጀመርኩት ገረፍ ገረፍ ንባብ (scanning) ሳላስበው እንደ ውኃ ሙላት ጎትቶ አስገብቶ በዚያው ሲያሳድረኝ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር። ንባቤን ከጨረስኩ በኋላ የመጀመሪያው ጥያቄዬ "እንዴት ሊጽፈው ቻለ?" የሚል ነበር። ምክንያቱም እኔ የማውቀው ዓለማየሁ ዋሴ (PhD) በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ የሥነ ምህዳር ባለሙያ (Ecologist) ነው። በርግጥ በምርምር ላይ ባስመዘገበው አዲስ ግኝትም ATBC(Association for Tropical Biological Conservation - የትሮፒክ አካባቢ ሥነ ሕይወት ጥበቃ ማኅበር) በየዓመቱ የሚያዘጋጀውን የ2007 (እ᎐ ኤ᎐ አ᎐) የአልወን ጀንትሪ ሽልማት (Alwyn Gentry Award) ያገኘ፣ በአሁኑ ጊዜም ከአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በምርምር የሚሠራና በዚያው ያሉ የሁለተኛ ዲግሪና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የሚያማክር፣ በየጊዜው የምርምር ሥራዎቹን በመስኩ ከፍተኛ ዕውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ የሚያሳትም፤ በአጭሩ በራሱ የሙያ መስክ ስመ ገናና ከሆኑት ተመራማሪዎች አንዱ እንደሆነ በደንብ አውቃለሁ። አንዳንድ ሥራዎቹን ለማንበብ፣ ሌሎች ተመራማሪዎች ስለእርሱ ከጻፏቸውም ጥቂቶቹን ለመየት ዕድሉን አግኝቻለሁ። ሆኖም በዚህ መልኩ ሥራ ይዞ ብቅ ይላል የሚል ግምት አልነበረኝም። ጥያቂዬ የተፈጠረው እንዲህ ዓይነት ባለሞያ ወደ ሥነ ጽሑፍ ድንገት ለምን ብቅ አለ ከሚል አልነበረም። እንደ አቅሜ በረዳኋት የሥነ ጽሑፍ ተማሪነቴ ወቅት ብዙ ጸሐፍት የሥነ ጸሑፍ ባለሞያዎች እንዳልሆኑ አውቃለሁና። ጥያቄና መደነቅ የፈጠሩብኝ ሁለት ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው ይዞት የተነሣው ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ግን አንድ በምርምር ሥራ አንቱ የተባለ ሰው፤ ብዙ ሥራዎችን ከማሳተም የተነሣም ያንን በምርምር ዘዴና በመርህ አብዝቶ የታሰረ የምርምር ጽሑፍ ቁጥብነትን ድንበር ተሻግሮ እንዲህ ዓይነት የትረካ ችሎታም በመጎናጸፉ ነው። ምንም እንኳ የትረካ ችሎታው ጥያቄም መደነቅም ቢፈጥርብኝም የምርምር ችሎታውና ከዚሁ ሥራው ጋር በተገኘ ያደረጋቸው ዓለም አቀፍ ጉዞዎች፤ የመስክ ሥራዎች፣ ገጠመኞችና ሌሎቹም ሁነቶች መጽሐፉን ከዋናውና አስደናቂው ታሪክ ባሻገር ብዙ አጫጭር ታሪኮችን እንዲያዋሕድ፣ የተለየ ጭብጥ እንዲያነሳ፣ የሰላ ሂስ እንዲያቀርብና ተወዳጅ አቀራረብ እንዲኖረው ያስቻለው ይመስለኛል። ስለዚህም ጥብቅ ሥራ ባቀዱ ቀን ንባቡን እንዳይጀምሩ እመክረዎታለሁ፤ ሥራዎን ረስተው ተመስጠው ከቀሩ በኋላ ሣልሠራ ቀረሁ እንዳይሉ እሰጋለሁና። ብርሃኑ አድማስ (ዲያቆን፣ በፊሎሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ)