እነዚህ መረጃዎች በረጅም እና በተለያየ ጊዜ በቃል ተሰጥተው የተገኙ በመሆናቸው መደጋጋምና እና አንዳንዶቹ ሲጣረሱ ሊገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ይኸን ከግለሰቡ <ፍኖተ ሕይወት>(የሕይወት ታሪክ) ጋር ማገናዘብን አስፈላጊ ያደርጋልና፣ አቀናባሪውን ከበድ ያለ ጥረትና ትጋት ሳይጠይቅበት የቀረ አይመስልም። ሆኖም፣ ለማሳከት አስመስጋኝ ጥረት ያደረገ መሆኑን ውጤቱ ያሳያል። ኤርምያስ ሁሴን ያቀናበረውንና፣ እሳት እና ውሃ ... በማለት ርእስ ሰጥቶ ያቀረበውን ይኸንን የጸጋዬ ገብረ መድኅን (ሮበሌ) ቀዌሳን፣ በየወቅቱ የተሰጡ የቃል ገለጻዎች ስብስብ የምናየውና የምንመዝነው በዚህ መልክና መንፈስ ነው።ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ<<ያልተተረከ ሕይወት ሊኖሩት የሚገባ አይደለም>> ይላሉ። ኤርሚያ ጸጋዬን ተረከው። የጸጋዬ ሕይወት ሊኖሩት የሚገባ ሕይወት መሆኑን አሳየን። ተረክ የትርጉም ማዳወሪያ ነው። ሕይወት ትርጉም የሚያገኘው በትረካ ነው። ለሕይወቱ ትርጉም ሰጠው። ተረክ የሌለው ሕይወት አድካሚ ነው። ትርጉም አልባ ነው። ሕይወት ከትረካ በሪት ምውት ነች። ከትረካ በፊት የተበታተኑ መስለው የሚታዩ ነገሮች፤ ከትረካ በኋላ መልክ ይይዛሉ። ከትረካ በፊት የምናየው ሕይወት፤ ዝሆንን በዳበሳ ለማወቅ ከሞከሩት ሦስት የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። ኩንቢውን የነካው፤ <<ዝሆን ግንድ የመሰለ ፍጥረት ነው>> ሲል፣ ጆሮውን የነካው <<ዝሆን ሰፌድ መሰል ነው>> ሲል፣ እግሩን የነካው ደግሞ <<ምሰሶ ይመስላል>> ይላል። ሁሉም ስሑት ናቸው። ትረካ የዝሆኑን ኩንቢ፣ ጥርስ፣ ጆሮ እና እግር አገናኝቶ የተሟላ ምስል ይፈጥርልናል።ስለዚህ ሕይወት ከትረካ በፊት እና በኋላ አንድ አይደለችም። ከትረካ በፊት ግዑዝ ነች። አናባቢ የሌለው ሆሄ ነች። ሕይወት አናባቢ የምታበኘው፤ በእዝነ-ሕሊና መደመጥ የምትችለው፤ በትረካ ነው። ስለዚህ ሕይወት ቅድመ ትረካ እና ድኅረ ትረካ አንድ አይደለችም። ትረካ ሁሉን በቦታው አውሎ ሙሉ ምስል የሚፈጥር ድንቅ የትርጓሜ ዐውድ ነው። ፈረንጆች፤ <<ማየት ግንኙነትን ማየት ነው>> ይላሉ። ግንኙነትን ማየት የሚቻለው በትረካ ነው። በየገጹ እና በየምዕራፉ የተበተነው የጸጋዬ መልክ በኤርምያስ ትረካ በአንድ ዐውድ ሲገባ ሙሉ ሥዕሉ ይፈጠራል። ኤርምያስ ሁሴን ይህን ሥራ ሠርቷል። በድምፅ የተመዘገበ ቃሉ ቀርቶበት ይሆናል እንጂ በጽሑፍ ሊያገኝ የቻለውን ሁሉ ለመሰብሰብ ሞክሯል። ጥሩ ጥረት አድርጓል።ኤርምያስ የጸጋዬን ምንባብ ሲሰራ፤ አንባቢን የሚገፉ ወይም የሚያገሉ፣ ለአዋቂ የሚያደሉ ነገሮች ያሉ ሲመስለው አደን ይሄዳል። ሥራውን የሚያግዙ ነገሮች ለማምጣት ሲሄድ የጸጋዬ ሥራ ክፍቱን ሊውል ይችላል። <<ሁሉ አማረሽ>> የሚያሰኝ አመል አለው። ንባቡንም ከባድ ያደረገው ይመስለኛል። ተመልሶ ሲመጣም እንደገና የጸጋዬን ድስት እፍ ብሎ ለማንደድ ይታገላል። ይባዝናል። ያባክናል። ዐ᎐ነገሩን ያረዝመዋል። ግን ልባም ለሆነ <<ታዳጊ አንባቢ>> የተሟላ ትርጉም እና መልእክት የያዘ ዐ᎐ነገር እንዲሠራ ያግዘዋል። ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረ መድኅን(ጸ᎐ገ᎐መ᎐)፤ <<ሥነ ግጥም ከመሠረቱ ያው የገዛ ሕይወቱ ሒስ ነው>> ሲል ማቲው አርኖልድ መናገሩን ይጠቅሳል። የጸጋዬም ሥራዎች የገዛ ሕይወቱ ሒሶች ናቸው።ተፈሪ መኮንንከአ᎐አ᎐ዩ᎐ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍክፍል(B.A.)ከአ᎐አ᎐ዩ᎐ ሶሻል አንትሮፓሎጂ ዲፓርትመንት(M.A.)