ሐዲስ ሣህሌ የዩኒቨርስቲ ትምህርት አቋርጦ ለአንድ ዓመት በማስተማር ራሱን ለመርዳት የተሠማራ ቢሆንም በገጠሩ ችግር ምክንያት ራሱን ለሕዝቡ እንዲሰዋ የተገፋፋ ወጣት ነው። ያለፈውን ትውልድ ሥራና ክንውን በማውጠንጠንና ከሚገባው በላይ ታላቅነቱን በማጋነን በትዝታ ተውጦ አይባክንም ። በትዝታ የሚባክን ትውልድ ፤ በራሱ የማይተማመን ፤ የሚኖርበትን ዘመን ችግሮች መቋቋም ያልቻለና መኖር ያቃተው መሆኑን የተገነዘበ ይመስላል ። ሐዲስ ለኢትዮጵያ አዲስ ፍጡር ነው። በወሬ አይፈታም ፤ ዓላማው በሙሉ ሠርቶ ለማሳየት ነው። መሰናክሎች ይገጥሙታል፤ ፈተና ይደርስበታል፤ ለሕይወቱ ያሰጋበትም ጊዜ ነበር። እንዴት ሊወጣው ቻለ?ጥንታዊውን ሳያሞካሽ ወይም ሳያንጓልል፤ ዘመናዊውንም ሳያጋንንና ሳያካኪስ በተደላደለ መንፈስ የቀረበ ውብ የሆነ ልብ ወለድ ጽሑፍ ነው። ከ'ከአድማስ ባሻገር' ይታይ የነበረው ወጣት፤ በኅሊና ደወል ከአድማስ ወዲህ ተከሠተ።