እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር በምትዘረጋው ቅድስት ሀገር ላይ የተቃጡ የጥፋት ተልዕኮዎችና ረቂቅ ተንኮሎች!!የግብፅ መኳንንት መምጣታቸው የማይቀር እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያም እጆቿን ወደፈጣሪዋ መዘርጋትዋ የሚጠበቅ ይሆናል። የግብፅን መኳንንት አስገዳጅ ሁኔታዎች ተቋቁሞ በፅናት ለማለፍ ግን ንቁ ሆኖ መጠበቅ ያስፈልጋል።በእዚህ የመጨረሻው ዘመን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከችግሩ መክፋት የተነሳ የውሸት ኑሮን እየኖረ በመጨረሻም የእውነት ሞትን የሚጋት ሆኖአል። ይህ መጽሐፍ ከወደቀባችሁ የእንቅልፍ እዚም በትንሹም ቢሆን ይቀሰቅሳችሁ እንደሆነ እንጂ በእዚህች ቅድስት አገር እየተካሄደ ያለውን ሥውር ርእሰ-ጉዳይ ላይ ጥቂት የፅሞና ጊዜ ወስዳችሁ በፀጥታ ውስጥ የሚመጣውን የዝምታ ድምፅ በአስተውሎት ለማዳመጥ ሞክሩ፤ ከውስጣችሁና ከእውነተኛ ማንነታችሁ እንደ ነጎድጓድ የሚያስገመግም እውነት በእለት-ተእለት ውሎአችሁ እያያችሁ ያላስተዋላችሁትን ምስጢር ፍንትው አድርጎ ያቀርብላችሁዋል።የግብፅ ፈርኦናዊ መንግስትና የአንግሎ አሜሪካ መንግስት የመጀመሪያውና የመጨረሻው የአለማችን ልእለ-ሀያል መንግስታት በመሆናቸው የተለየ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው እንዲሆኑ አድርጎአቸዋል። እንደ ዳንኤል ትንቢት (2:34-45) እንደ ኢሣይያስ ትንቢት (13:1-16) እንደዚሁም እንደ ዮሐንስ ራዕይ ትንቢት (ራእይ 16:12-16) ለአርማጌዶን ጦርነት መከሠት ምክንያቱ እግዚአብሔር የምስራቅ መንግስታትን የሚያስነሳ መሆኑ ነው። የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣትም ሆነ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትራምፕ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ለአርማጌዶን ጦርነት መፈንዳት መጠነኛ ፍንጭ ይሠጠናል።