ሥነግጥም ታስቦበት በስርዓትና በጥበብ የሚከናወን "አመጽ" ነው። ይህን አመጽ ማጥናት "አዲስ ስርዓት" የመትከልን፣ ግጥሙን መልሶ የመፍጠርን ያህል ፈታኝ ተግባር በመሆኑ ላብን፣ ምናባዊ ብቃትንና ነጻነትን ይጠይቃል። ግጥምን በወጉ ማንበብ ሙዚቃን፣ ስዕልንና ቅርጽን በግጥም ውስጥ አድምጦ፣ ተመልክቶና ዳብሶ ማድነቅ ማለት ነው። በዚህ በጥበቡ ባሕርያት ጸናናነት ምክንያት ይመስለኛል በአገራችን ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም የሥነግጥም ማስተማሪያ መጻሕፍት እንደልብ የማይገኙት። ካሉትም ጥበቡን የሚገሩና የሚያለምዱ፣ አንባቢን መማረክና ማሸነፍ የሚችሉ ጥቂቱ ብቻ ናቸው። ይህ የብርሃኑ መጽሐፍ ከእነዚህ አንዱ የሚሆን ይመስለኛል᎐᎐᎐ ብርሃኑን በመጀመርያ ተማሪው ሆኜ፣ በኋላም በጓደኝነትና በስራ ባልደረባነት አውቀዋለሁ። ይህ እውቀቴም ብርሃኑ በሥነጽሑፍ ላይ የሚያካሂዳቸውን ምርምሮች በቅርበት እንድከታተል አስችሎኛልና የአማርኛ ሥነግጥም የዚህ ልምዱና ምርምሩ ውጤት መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። መጽሐፉ በአማርኛ የሥነግጥም ትምህርት ያለውን ክፍተት ይሞላል᎐᎐᎐የመተንተኛና የመተርጎሚያ ብልሃቶቹ ተጨባጭ በመሆናቸው፣ ገጣምያን ግጥሞቻቸውን በእውቀትና በንቃት ለመከየኛነት፣ አንባብያንም በወጉ አንብበው ለማጣጣምያነ ት ሊገለገሉባቸው ይችላሉ። ትንታኔዎቹና ትርጓሜዎቹ በምስል የተሞሉ ናቸው፤ አይናገሩም፤ አይዘረዝሩም፤ አያብራሩም። ይልቁኑ ልክ እንደግጥሞቹ ባለ መንገድ ይስላሉ፤ ይቀርጻሉ፤ ያሳያሉ። ስለዚህ ዘና ማድረግ ኪናዊ እርካታን መስጠት የመጽሐፉ ሌላው ተግባር ይመስለኛል።ቴዎድሮስ ገብሬበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሥነጽሑፍ መምህርክዋኔ የሥነግጥም ህይወት መሆኑ ይታወቃል። ብዙዎቻችን ወጣቶች የቀደምት ገጣሚዎቻችንን የግጥም ክዋኔ ለማየት አልታደልንም። ይሁንና ብርሃኑ በዚህ መጽሐፍ፣ ግጥሞቹን ከነኪናዊ ምልዐታቸው እንድናውቃቸው ክዋኔ-አከል ተጨባጭና ምናባዊ ትንታኔዎችን ለኛም ሆነ ለታላላቆቻችን በሚደርስ መልኩ አቅርቦልናል። መጽሐፉ ለምሁራዊ ተብሰልስሎት (intellectual exercise)፣ ለትምህርታዊ ፋይዳና ለምናባዊ እርካታ እንደየመጥለቂያችን የምንቀዳበት የአማርኛ ሥነግጥም ባሕር ነው። በተለይም ለኛ ለወጣቶች ከአባቶቻችን የሥነግጥም ጥበብ ሊያጋባን የሚችል የነገር አባት ነው።ነቢዩ ባዬበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የትያትር ጥበባት መምህርየሀገሬ ሰው ገጣሚ ነው፤ ከንጉሱ እስከ እረኛ። ለዚህም ሃይ ሎጋው፣ ሙሾው፣ ጌረርሳው፣ ቀረርቶው፣ ሂያሴው᎐᎐᎐ ህያው ምስክሮች ናቸው። አሁን አሁን ደሞ በሕትመት የሚደርሱን ግጥሞች ብዛት መጨመር እጁጉን አስደሳች ነው። ይሁንና ግጥሞቻችን ለምን፣ በምን፣ ከምንና እንዴት ነው የሚሸመኑት? እንዴትስ ነው፣ ልናደምጣቸውና ልናደንቃቸው እምንችለው? የብርሃኑ መጽሐፍ እነዚህን ለመሳሰሉ ግጥሞን አንብቦ ከመረዳት ጋር ለሚዛመዱ ገራገር፣ ግን ውስብስብ ጥያቄዎች በምርምር የተገኙ ምላሾችን ይሰጣል። በመሆኑም፣ የአማርኛ ሥነግጥምን ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግጥማዊ ባህሎችና ግጥሞች መረዳት ለሚሹ ሁሉ ጠቃሚ መሳሪያ ይመስለኛል።አብርሃም ዓለሙበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአማርኛና የአፋን ኦሮሞ ሥነጽሑፍ መምህር