እነሆ፤ ነፍሴን ከሥጋየ ነጥዬ ከህዝብ ጋር ቀላቀልኳት!ከውስጥ ገጾች<<... ያ ሰሜን ኢትዮጵያ፤ የጥንታዊ ስልጣኔ መነሻ፤ የውጭ ወራሪዎች በየዘመናቱ አንገታቸውን ብቅ እያደረጉ ሲሰልሉት፣ እየወደሙም ቢሆን ሲወድሙበት የኖረ የዘመናት የጦር አውድማ! ያ ሰሜን ኢትዮጵያ፤ የውጭ ወራሪዎች በፈጠሩት መዘዝ ወንድም ከወንድሙ እየተጋጨ ሲተራረድ፤ አንተም ተው አንተም ተው የሚል ጠፍቶ የእርስ በእርስ መጨራረሻ የሆነ የደም መሬት! ያ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ወንድ ልጇን ያላስገበራት ኢትዮጵያዊ እናት የለችምና የወላድ እርግማን የደረሰበት ይመስል ቦምብና መትረየስ እየወረደበት፣ አጥንት እየተከሰከሰበት፣ የሰው ልጅ አስከሬን በአውሬ እየተጎተተበት፣ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ የወደፊት ዕጣ ፋንታው እንኳ ገና በውል ያልታወቀ የሀገር ክፋይ! ታዲያ ... እንዴት ሆኖ ...>>***<<.... ማስተዋል የጎደላቸው እብሪተኞች ስልጣን በያዙበት ጊዜና ቦታ ሁሉ አውቆ መገኘትን ያህል የማይድን በሽታ የለም። መሰሪ አካሄዳቸው በገባህ ቁጥር ልብህ ይደማል። ሲዋሹና ሲቀጥፉ በሰማህ ቁጥር አንጀትህ ይቆስላል። የጭካኔ ተግባራቸውን በምታይበት ጊዜ ውስጥህን ይኮሰኩሰዋል። ያኔ መንፈስህ ይረበሽና አካላዊ ጤናም ታጣለህ፡ ያልታደለች ሀገር ዜጋ ከመሆን የሚመነጭ አለመታደል! ስለዚህ...>><<እኔ አልኮነንም ሀሰት ተናግሬ፤እኔ አልታመም ውሸት ተናግሬ፤ድሃ አልኖረብሽም ድሃዋ ሀገሬ።ሰዎች ኡኡ በሉ ምነው ዝም አላችሁ፤ወገኖቼ ጩሁ ምነው ፀጥ አላችሁ፤ግፍ ራስ አዙሮ ሲጥል እያያችሁ።እኛ በከንቱ ሞተናል፣ "እናንተ ግን አደራ ራራራራራ.....">>