᎐ ከወዲያነሽ ደራሲኃይለ መለኰት ማጀቴን ከነገበያዋ፥ ከነአማርኛዋ ቁጭ አርጓታል። አይ አማርኛው ማማሩ! ወለል ብላ በምትታየን ማጀቴ የሚኖሩት ገፀ-ባህርያት በሕይወት ያየናቸውና ያወቅናቸውእንጂ በልቦለድ ውስጥ ያነበብናቸው አይመስሉም ። ምንዳ እና ልክየለሽ ባልና ሚስት ናቸው -- አቤት ሲዋደዱ! እንደዚህ ዓይነቱን እውነተኛ ፍቅር በልቦለድ ውስጥ ካነበብኩ ብዙ አመት ሆነኝ ። ታዲያ እየተዋደዱም መለያየት መነፋፈቅ አለ -- ኑሮ አስቸጋሪ ነዋ።ምንዳና ቸርነት ጓደኛሞች ናቸው ። በጓደኝነት ውስጥ ምን ያህል ጥልቀትና ጽናት ሊኖር እንደሚችል በነዚህ ሰዎች አየሁ። የዳዊትንና የዮናታንን ጓደኝነት አስተወሰኝ -- የፍቅራቸው ለዛ ።ወይዘሮ እልፍይከንዱ የቀኛዝማች ሚዝት ፥ ወይዘሮ ደጅይጥኑ ደግሞ ቅምጥ ናቸው። እነሆ ጣውንትነት።አፈሳ የምንዳ ባላጋራ ነው ። አይ ተንኮሉ! ደሞ ሲፈራስ! ልቦለድ ውስጥ የፈሪ ነብስ እንደ ዛሬ ራቁቷን ታይታኝ አታውቅም ።ትረካው ፈጣን ፥ ቋንቋው እንከን አልባ ፥ ገጸ--ባሕርያቱ ጉልህ ናቸው ። ልቦለድ ይሉዋችኋል ይኸ ነው! መጻፍ ካልቀረ እንዲህ ነው ። ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር