በርግጥ ያንን የኢትዮጵያ የመንፈስ ልእልና መመለሱ ይበጃል፤ ግን የኢትዮጵያውያንን፣ የህዝቦቿን የነጠረ እውነት የሚኖሩትን ህይወት - የፀኑበትን ሀይማኖትና እምነት - የሚጋሩትን ዜግነትና እሴት ...ወዘተ. ተጨባጭ ህልውናዋን መሰረት እንዲያደርግ ማድረግ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የምንኖራት ተጨባጭ እውነት፣ ኢትዮጵያዊነትም እንደሀይማኖት ያለጥያቄ የምንቀበለው ሳይሆን፣ ከዚሁ ተጨባጭ ኑሯችን የሚመነጭ፣ እንደእውቀት ኖረን የምንመረምረው፣ ከዘመን ጋር የምንሞርደው መንፈስ መሆን አለበት። (የትኛዋ ኢትዮጵያ)..........እዚህ ላይ መመልከት ያለብን ማህበረሰባችን የስነምግባር እንክርዳድ ለማምረት የተመቸ ማሳ እንደሆነ ነው። በደርግ ዘመን ኬላ ላይ በመቶዎች የሚቆጠር ብር እየተቀበለ ኮንትሮባንድ የሚያሳልፈው ፊናንስ ፓሊስ፣ (በዘመነ ቀዳማይ ኢህአዴግ) በምን ፍጥነት የሀገርን ድንበር ጥሶ፣ በጦር ሠራዊት መኪኖች ኮንትሮባንድ ወደሚነግድ፣ ዶላር በሻንጣ ከሀገር ወደሚያወጣ ጀነራል እንዳደገ ስንመለከት፣ ማህበረሰባችን ምን ያህል ለስነምግባር ዝቅጠት ተስማሚ እንደሆነ እናስተውላለን።. . . . . አንድ ማህበረሰብ ገሚሱ ወንጀል ፈፃሚ፣ ገሚሱ አጨብጫቢ፣ ገሚሱ በዝምታ ታዛቢ ሆኖ እንዲህ አይነቱን ወንጀል ከተፈጸመ፣ ህግ መሰረቷ ከድቷታልና አስፈጻሚ አታገኝም፤... ሰው ሲቃጠልና፣ ሰው ዘቅዝቆ ሲሰቀል፣ ኳስ እንደሚያይ ተመልካች ከብቦ የሚታዘብ ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ በስነምግባር ዘቅጧል። ያንን ዜና ሰምቶ፣ ቤቱ ገብቶ ተኝቶ ያደረው የማህበረሰብ ክፍልም ወንጀሉን ካጀበው አይለይም፤ ወንጀለኞቹን አቅፎ፣ አብረውት እንዲኖሩ ተቀብሏልና እንደ ማህበረሰብ በስነምግባር ዘቅጠናል። (ማህበረሰባዊ የስነምግባር ዝቅጠት)..........አሁን ባለው ሁኔታ አማርኛ ላይ ኦሮምኛን በመጨመር ሁለት የፌደራሉ ኦፊሻል ቋንቋዎችን መገልገል ተገቢ ነው።... የአማርኛና የኦሮምኛ ቋንቋዎችን የፌደራሉ መንግስት ኦፊሻል የስራ ቋንቋ መሆን እንደመጨረሻ ግብ መወሰድ የለበትም፤ እነዚህ ሁለት ቋንቋዎች 63.1 በመቶ የሆነው የአፍመፍቻ ተናጋሪ ብቻ ያቀፉ ናቸው። ... ከሁለቱ ቋንቋዎች የፌደራል ኦፊሻል የስራ ቋንቋነት ትግበራ ልምድ እየተወሰደ፣ ተጨማሪ ቋንቋዎችን ወደ ፌደራል የስራ ቋንቋነት ማሳደግ ተገቢ ነው። በሚቀጥሉት ከ15 እስከ 25 ባሉት አመታት፣ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ ብዛት ውስጥ ከ5 በመቶ በላይ የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ያላቸው ሶማሊኛ፣ ትግርኛና ሲዳምኛ በፌደራል ደረጃ ኦፊሻል ቋንቋዎች ቢደረጉ፣ 63.1 በመቶ የነበረውን የፌደራል ኦፊሻል ቋንቋዎች የአፍመፍቻ ተናጋሪ ብዛት ወደ 80 በመቶ ያስጠጋዋል። ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች የሚናገሩ፣ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚኖሩባት ሀገር፣ አምስት ቋንቋዎችን የፌደራል የሥራ ቋንቋ በማድረግ የ80 በመቶ ዜጎችን ማካተት ለአንድ ሀገር የቋንቋ ፓሊሲ ከፍተኛ ስኬት ነው። ይህ በተራው ዜጎች አዎንታዊ ሀገራዊ የጋራ አመለካከት እንዲያዳብሩ በማድረግ፣ የሀገር ግንባታ ሂደትን ያሳልጣል። (የትኛው ቋንቋ)